በጅማ ዩኒቨርስቲ ጥቅምት 28 ቀን 1998 ዓ.ም. የተከሰተውን የተማሪዎች ችግር ለመፍታት እና ትምህርት እንዲጀመር ለማድረግ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ እና የትምህርት ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር በስፍራው በመገኘት ተማሪዎችን ለማደራደር እየጣሩ መሆኑ ተሰማ። ሆኖም ትምህርቱ እስካሁን አልተጀመረም።
ከኦሮሚያ የጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በዩኒቨርስቲው የተከሠተው ግጭት በሁለት ተማሪዎች አለመግባባት የተነሳ ሲሆን ቀስ በቀስ ወደ ቡድን ግጭት ማምራቱን ያመለክታል።
በሁለት ተማሪዎች መካከል የተነሳው ጠብ ሊሰፋ የቻለው ሌሎች ተማሪዎች ተቀላቅለውት የብሄር ስሜት መንፀባረቅ በመጀመሩ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። በዚህም ምክንያት በተለይ በዩኒቨርስቲው ሕንፃ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።
የኦሮሚያ የፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ እውነቱ ብ.ደበላ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ይህንን ችግር ለመፍታት የት/ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር እናን የኦሮሚያ የፀጥታ አስተዳደር በስፍራው በመገኘት ተማሪዎቹን ለማስማማት ጥረት እያደረጉ መሆኑን በመግለፅ ለችግሩ መንስኤ የሆነውን ጠብ ጭረዋል የተባሉ ሁለት ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ጉዳያቸውም በህግ እንደሚታይ አረግጠዋል።
አንዳንድ ተማሪዎች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት የተጋጩት ሁለት ቡድኖች ለማስማማት እየተደረገ ያለው ጥረት እስካሁን ያልተሳካ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች በግቢው ያለ የኦሮሚያ ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት እንዲወጣ በመጠየቃቸው ነው ብለዋል።
የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ግን የተማሪዎቹን ቅድመ ሁኔታ ባለመቀበሉ ድርድሩ ችግርን እንደገጠመው እንዲሁም በርካታ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ከግቢው በመለቀቃቸው ችግሩን ለማቃለል እና ትምህርት ለማስጀመር አለመቻሉን ገልፀዋል።
«የመከላከያ ሰራዊት በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ እንዴት ሊገባ ቻለ?» በሚል ለኦሮሚያ የፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ላቀረብነው ጥያቄ የመከላከያ ሠራዊት በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ በጭራሽ አለመግባቱን ገልፀው ይሁን እንጂ ችግሩ በአካባቢው ከሚገኘው የፖሊስ ኃይል አቅም በላይ በመሆኑ ምክንያት በፌዴራል ፖሊስ ስር ግቢ እንዲገባ መደረጉን አረጋግጠዋል።
ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ባለፈው ማክሰኞ እለት ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት በኦሮሚያ የተፈጠረው ግጭት ከክልሉ አቅም በላይ ባለመሆኑ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ ገብነት የጠየቀበት ሁኔታ የለም ማለታቸው ይታወሳል።