የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ አመራር አባላት በማረሚያ ቤት ቦታ ጥበቅ ምክንያት አሁንም በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መምሪያ ናቸው። በሌላ በኩል የቅንጅት ሊቀመንበር ኢ/ር ሃይሉ ሻውል በሕመም ምክንያት ፖሊስ ሆስፒታል በህክምና ላይ ይገኛሉ።
ሕዳር 22 ቀን እና ከዚያ ተከታታይ ቀናት ባሉት ጊዜያት ከእነ ኢ/ር ሃይሉ ሻውል መዝገብ ሌላ ባሉ መዝገቦች ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ ምርመራዬን ጨርሻለሁ ምግብና መኝታ ወዳለበት ይዛወሩልኝ ሲል የጠየቀ ቢሆንም ታህሳስ 7 ቀን በዋለው ችሎት ላይ በቦታ ጥበት ምክንያት ወደ ማረሚያ ቤት ሳይዛወሩ መቆየታቸው ተገልጿል።
የቅንጅቱ አባል የሆኑት አቶ አቶ በድሩ አደም በዕለቱ እንደገለጹት በማረሚያ ቤት (ቃሊቲ) ብንሆን ኖሮ ከጠበቆቻችን ጋር በሰፊው ለመነጋገር እናገኝ የነበረው መብት አሁን ባለንበት ቦታ ማግኘት አለብን። ሲሉ ጠይቀዋል።
ፍ/ቤቱ ባለፈው ጊዜ የተከሳሾቹ ጠበቆች ባሉበት ይቆዩልን ወደ ማረሚያ ቤት አይሂዱብን በሚል የጠየቁትን አስታውሶ የዓቃቤ ሕግን አስተያየት ጠይቋል።
ማረሚያ ቤት በተፈጠረ የቦታ ጥበት ምክንያት መቆየታቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጾ «አሁንም ቢሆን እኛ እንልካቸዋለን» ብሏል።
ፍ/ቤቱም ከዚህ በኋላ በስፋት ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት ስላለባቸው ሁኔታውን እንዲስተካከል አዟል።
የቅንጅቱ ሊቀመንበር ኢ/ር ሃይሉ ሻውል በሕመም ምክንያት ከማክሰኞ ታህሳስ 4 ቀን ጀምሮ በፖሊስ ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ በመሆኑ በቀጠሮው እለት ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
በተያያዘም አርቲስት ደበበ እሸቱ ማክሰኞ ታህሳስ 4 ቀን በነበራቸው የኦፕራሲዮን ቀጠሮ የጥበቃ ኃላፊው ሳይፈቅድላቸው በመቅረቱ ህክምና ሳያገኙ እንደቀሩ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።
የጥበቃ ሃላፊው ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሁኔታውን ለአለቃቸው እንዳስታወቁ አለቃቸው ደግሞ የሚመለከተውን ሰው ላነጋግር ማለቱን እና የሚቀጥለው ማክሰኞ ይሄዳሉ መባላቸውን ገልጸዋል።
ፍ/ቤቱ የህመም ጉዳይ ፋታ የሚሰጥ ባለመሆኑ በአስቸኳይ ህክምናውን እንዲያገኙ አዟል። በተያያዘ ዜና በእስር ላይ ያሉ የቅንጅት አመራር አባላት የጀመሩትን የረሃብ አድማ እንዲያቆሙ ከኢሰመጉ በተጻፈ ደብዳቤ ቀረበላቸው።